የኢትዮጵያ እንስሳት ሃኪሞች ማህበር አመታዊ ጉባኤውን ህዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም በበይነ መረብ አማካኝነት አከናውኗል፡፡ ጉባኤው ተፈጥሯዊ የአደጋ ስጋቶች በእንስሳት ሐብት እና ጤና ላይ ያላቸው ተፅእኖ በሚል መሪ ሃሳብ ተከናውኗል፡፡ በጉባኤው ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች እና ከተደረጉት ጥልቅ ውይይቶች በመነሳት የሚከተሉት አንኳር ሃሳቦች ተለይተዋል፤
- የእንስሳት ጤና ጥበቃ አገልግሎት ሁለንተናዊ ይዘት ያለው ከመሆኑ አንፃር በሞያው የተሰማራን ባለሙያዎች ሁሉ የህብረተሰብን፣ የእንስሳትንና የአካባቢን ጤና ከመጠበቅ አንፃር ግንዛቤ እንደተፈጠረ ይታመናል፡፡ ስለዚህ የአንድ ጤና ፍኖተ ካርታ (One Health) ተግባራዊ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ከግብርና ና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤቶች፣ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና እንዲሁም ከአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ጋር በተቀናጀ መልኩ መስራት ይጠበቃል፡፡
- በሀገራችን የተከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የእንስሳት ሀብት ላይ ያደረሱትንና ሊያደርሱ የሚችሉትን ተፅዕኖዎች በይበልጥ ለማወቅ እና ለማረጋገጥ፣ በማስረጃና በእውቀት (Evidence and knowledge based) ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ ተከታታይና ጠንካራ የቅኝት ስራዎችን እንዲሁም ጥናቶችንና ምርምሮችን በተቀናጀ መልኩ ማካሄድ ተገቢ ይሆናል፡፡
- የእንስሳት ሐብት ልማት በተለይም የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች የሀገሪቱን የአደጋ ስጋት አመራር ስርዓት (Disaster Risk Management Framework) በተለይም የእንስሳት ሐብት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ስርዓት ጋር ለምሳሌ እንደ Livestock early warning እና Livestock Emergency Guidelines/ ራስን ማስተዋወቅና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ እንደ ሀገርም የDRM policy እና Livestock Development and Emergency ሥርዐትን ማወቅ እና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ቀደም ሲል የተዘጋጀውን የእንስሳት ሐብት ልማት የአደጋ ጊዜ ማኑዋል መከለስ አስፈላጊ በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና ከሌሎች የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባር መከለስ፣ማስተዋወቅ እና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
- የእንስሳት ሀብት ልማት ወይም የህክምና ባለሙያዎች በሀገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱና ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን በመለየት እንስሳት አርቢው፣ የግል ዘርፉ፣ ማህበረሰቡ የቅድመ ጥንቃቄ እንዲወስድ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን፣ ምክከሮችን፣ በየወቅቱ ማካሄድ እና ውጤታቸውን መገምገም ጠቃሚ ይሆናል፡፡
- የእንስሳት ህክምናና ሌሎች የእንስሳት ሐብት ልማት ባለሙያዎች በዚህ ዓመት የተከሰቱ የተፈጥሮ ክስተቶችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከሰለጠኑበት ሞያ ውጪ የሚፈለግብንን እውቀትና ልምድ ማዳበር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ራሳችንን ካለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ከሚመጡ ድንገተኛ ክስተቶች (Emerging diseases, Natural disasters) ጋር የራሳችንን ትንበያ በማድረግ በምናገኘው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ያለንን ልምድ፣ እውቀት እና ክህሎት ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡
የእንስሳት ህክምና አገልግሎት የድርቅ እና ሌሎች መሰል አደጋዎችን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የእንስሳት ህክምና ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ድርቅን የመቋቋም እና ዘላቂ ልማትን ማጎልበት ላይ በተጀመሩ ስራዎች በግብርና፣ በውሀ ሀብት፣ በሰላም፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም መስኮች የተጀመሩ ስራዎችን ትኩረት በመስጠት ያሉትን ችግሮች በማወቅ በምንሰራበት ተቋም (ሴክተር መ/ቤት) የ Contingency plan በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲሆን እና ሞያዊ ድርሻ መወጣት ያስፈልጋል፣ የሚል ምክረ ሐሳብ የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማህበር ያቀርባል፡፡