Condolence

ዶ/ር ፍቃዱ ከበደ (1954-2016 ዓ.ም)

ዶ/ር ፍቃዱ ከበደ መንገሻ በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱ እና በሙያቸው የተከበሩ የእንስሳት ሀኪም ነበሩ፡፡ የዶክትሬት ድግሪያቸውን በቀድሞ ሶቪየት ዩክሬን እና የማስተርስ ዲግሪያቸውን በማይክሮባዮሎጂና ተዛማች በሽታዎች ምርመራ ቴክኖሎጂ በፈረንሳይ ሀገር አግኝተዋል፡፡ ከሰሩባችው ተቋማት መካከል፡-

1981-1983 ቦረና አውራጃ በእንስሳት ሀኪምነት
1984-1992 በኮምቦልቻ ላቦራቶሪ ተመራማሪ የተዛማች በስታዎች ቅኝትና ምርመራ ሀላፊ በመሆን ለፓን አፍሪካን የደስታ በሽታ የማጥፋት መርሀግብር ስኬት የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡

1993-2007 ዓ.ም በብሔራዊ የእንስሳት ኢንስቲትዩት የምርምር ላቦራቶሪ ዳይሬክተር በመሆን በጡረታ እስከተለዩበት ዘመን በትጋት አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ የተለያዩ የምርመር ፅሁፎችንም አበርክተዋል፡፡ ሚያዝያ22 2016ዓ.ም በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል፡፡
ዶ/ር ፍቃዱ ከበደ የኢትዮጵያ እንስሳት ሃኪሞች ማህበር ነባር አባል እና ለረጅም አመታት የቆዩ ማህበሩን ጠብቀው ካቆዩ አባቶች አንዱ ነበሩ፡፡ የኢ.እ.ሃ.ማ ጆርናል አስር የህትመት ቅፆችን ወደ ኤሌክትሮኒክ ኮፒ ሲቀይር በስራው የተሳተፉ, በማማከር ያገዙ እና ሌሎች ለማህበሩ አስተዋፅኦ የነበራቸው የተከበሩ ዶ/ር ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ እንስሳት ሃኪሞች ማህበር እኚህን ታላቅ የሙያ አባት በማጣቱ የተሰማውን ሀዘን ለመግለፅ ይወዳል፡፡
ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለስራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡

ዶ/ር አሰግድ ሽፈው  

ዶ/ር አሰግድ ሽፈራው የተከበሩ የእንስሳት ሀኪም የነበሩ የዶክትሬት ድግሪያቸውን በቀድሞ ሶቪየት ዩክሬን ለ 5 ዓመታት ከተከታተሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የእንስሳት ህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1979 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን በቬተሪናሪ ፐብሊክ ሄልዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጥንተዋል፡፡

ከሰሩባችው ተቋማት መካከል በምስራቅ ጎጃም በግብርና የእንስሳት ጤና ሃላፊ ሁነው ሰርተዋል እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር በደረቅ አካባቢዎች የኤክስቴንሽን መምሪያዎች ከፍተኛ የእንስሳት ሀኪምነት፤ የኳረንቲን እና ስጋ ምርመራ ከፍተኛ ባለሙያነት እና በአማካሪነት ስራ ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን፤ ለተለያዩ ተቋማት የማማከር አገልግሎት በግል ሲሰጡ ቆይተው ባደረባቸው ህመም ሰኔ 8 2016ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል፡፡

ዶ/ር አሰግድ ሽፈራው የኢትዮጵያ እንስሳት ሃኪሞች ማህበር ነባር አባል፤ለረጅም አመታት ማህበሩን ጠብቀው ካቆዩ እና በማህበሩ ኮንፍረንሶች ላይ የላቀ ተሳትፎ ከነበራቸው ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ በተለያዩ ኮሚቴዎች እና የአባላት ተሳትፎን በሚጠይቁ የማህበሩ ስራዎች ላይ የበኩላቸውን ያበረከቱ የሙያው ፍቅር ያላቸው አባት ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ እንስሳት ሃኪሞች ማህበር እኚህን ታላቅ የሙያ አባት በማጣቱ የተሰማውን ሀዘን ለመግለፅ ይወዳል፡፡

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለስራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡

ዶ/ር አበበ በሪሁን ጎበዜ 1969 – 2017 ዓ.ም

ዶ/ር አበበ በሪሁን ከአባታቸው ከአቶ በሪሁን ጎበዜ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብታድጌ አበጀ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ህንቦ ወረዳ ግንቦት 5/1969 ዓ/ም ተወለዱ። ከ1ኛ- 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የተማሩ ሲሆን ከ9-12ኛ ክፍል ደግሞ በአቃቂ አድቨንቲስት አዳሪ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከዚያም በእንስሳት ህክምና የዶክተርነት ድግሪያቸዉን በ1997 ዓ/ም እንዲሁም የማስትሬት ድግሪያቸውን በ2017 ዓ/ም በቨተሪናሪ ፓራሲቶሎጂ ከአድስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

ከሰሩባቸው ተቋማት መካከል፡

ከ2000 ዓ/ም እስከ 2010 ዓ/ም በአላጌ ግብርናና ቴክኒክ ኮሌጅ በከፍተኛ ኢንስትራክተርነት ሙያ እና ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ህይዎታቸው እስካለፈበት ድረስ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማስተማር፣በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት በቅንነትና በታታሪነት ተቋማቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው ባጋጠማቸው ድንገተኛ አደጋ በተወለዱ በ48 ዓመታቸው መስከረም 6/2017 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። ዶ/ር አበበ በሪሁን ለትንሽ ትልቁ መካሪ፣ ለሕጻናት ልዩ ፍቅር ያላቸው፡ ቅን፣ ስራቸዉን ወዳድ፣ ታታሪና ሰዓት አክባሪ ነበሩ። ለቤተሰባቸው፣ ለስራባልደረቦቻቸውና ለተማሪዎቻቸው መጥስናናትን እንመኛለን።

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለስራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡

ዶ/ር አካሉ ከበደ 1976 – 2016

ዶ/ር አካሉ ከበደ ረታ ከአባታቸዉ ከአቶ ከበደ ረታ እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ አልማዝ ሲራጅ በቀድሞዉ አጠራር በኢሉባቡር ክ/ሀገር መቱ ከተማ ነሃሴ 25/1976 ዓ.ም ተወለዱ። ዶ/ር አካሉ ከበደ እድሜያቸዉ ለትምህርት ሲደርስ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በጋምቤላ ራስ ጎበና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ትማህርታቸዉን ተከታትለዋል። ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በጋምቤላ መለስተኛ 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዉ ከፍተኛ ዉጤት በማምጣት ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም ለ6 ተከታታይ አመታት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና በዶክትሬት ድግሪ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን (DVM) አግኝተዋል።

ዶ/ር አካሉ ከበደ በተማሩበት የሞያ ዘርፍ ወደ ተማሩበት ክልል በመምጣት የክልሉን ምህበረሰብ በክልሉ በቀድሞዉ ግብርና ልማት ቢሮ የእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት ቢሮ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዳሬክቶሬት በመሆን እያገለገሉ ህይወታቸዉ እስካለፈበት ድረስ ቆይተዋል። ዶ/ር አካሉ ከበደ ባለ ትዳርና የአንድ ወንድ እና ሴት ልጅ አባት ነበሩ። ዶ/ር አካሉ ከበደ በተወለዱ በ40 አመታቸዉ ነሃሴ26/2016 ዓ.ም በድንገተኛ አደጋ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለስራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡

Scroll to Top