በኮረና ቫይረስ (COVID-19) በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ዙሪያ ከኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማሕበር የተሰጠ የድጋፍ መግለጫ እና ምክረ-ሐሳብ

በኮረና ቫይረስ (COVID-19) በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ዙሪያ ከኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማሕበር የተሰጠ የድጋፍ መግለጫ እና ምክረ-ሐሳብ

በኮረና ቫይረስ (COVID-19) በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ዙሪያ ከኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማሕበር የተሰጠ የድጋፍ መግለጫ እና ምክረ-ሐሳብ

በመጀመሪያ በአሁኑ ሰዓት በስፋትና በፍጥነት በመሰራጨት ዓለማችንን እያስጨነቀ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኢ.ፌ.ደ.ሪ መንግስት በተለይም የጤና ሚኒስቴር እየወሰዱ ያለውን ፈጣን እርምጃዎችና ቁርጠኝነት የተሞላበት ተግባራት የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማህበር ያለውን አክብሮትና አድናቆት ለመግለፅ ይወዳል፡፡

እንደሚታወቀው የኮሮና ቫይረስ በአለማችን ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እያጠቃና ከ120 ሺህ የሚበልጡ ዜጎችን ለሕልፈተ-ሕይወት ከመዳረጉም ባሻገር፤ ወረርሽኙ አድማሱን እያሰፋ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማሕህበራዊ ቀውስ በማስከተል ላይ እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርት መረጃ ያመለክታል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በሽታው መከሰቱ ከተረጋገጠ ጀምሮ እያስከተለና ወደፊትም ሊያስከትለው የሚችለውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ  ከግምት ውሰጥ በማስገባት በመንግስት ከወዲሁ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና በጤና ባለሙያዎች፣ ማህበረሰቡና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየትደረገ ያለው ርብርብ ይበል የሚያስብሉ ናቸው፡፡ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይበልጥ የተሳኩ ከማድረግ አንፃር የተለያዩ አጋር አካላት እንዲሁም የህብረተሰቡን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቁ እንደሆኑ ማህበራችን ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም ማህበራችን በአሁን ሰዓት መንግስት በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከመደገፍም ባገሻገር ሙያችን የሚጠይቀውን አበርክቶት ለመደገፍ ዝግጁነታችንን እየገለፅን ለሚደረገው ርብርብ አስተዋፅኦ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

  1. በአለማችን በአሁን ሰዓት የአንድ ጤና መድረክ (One Health Approach) የተለያዩ ሙያዎች የጋራ ጥምረትን መሰረት ባደረገ መልኩ ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮችን ለመፍታት ተመራጭ መንገድ ሆኖ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በሀገራችንም ያለውን እምቅ እና የተሰባጠረ የባለሙያዎች ሀብት ወደ ተግባር በማስገባት የኮረና ቫይረስ በሽታ ቁጥጥር ማጠናከር እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በዚህም ረገድ የጤና ሚኒስቴር፤ በግብርና ሚኒስቴር ስር ከሚገኘው  የእንስሳት ጤና አገልግሎት፤ የብሔራዊ የእንስሳት በሽታ ምርመራና ጥናት ማእከል፤ ብሄራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩትና የክልል እንስሳት ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሙሉ፤ የኮረና (COVID-19) በሽታን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በጋራ የሚሰሩ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ እየተደረገ ላለው የበሽታ ቁጥጥር የበኩሉን ጉልህ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ማህበራችን የሚያምን ሲሆን የትብብር አድማሱን ይበልጥ እንዲያሰፋና እንዲያጠናክር የኢ.እ.ሐ.ማ ይመክራል፡፡ በተለይም የብሔራዊ የእንስሳት በሽታ ምርመራና ጥናት ማእከል በሚደረገው የኮረና ቫይረስ ምርመራ ሂደት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችል ይታመናል።
  1. የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ከመግታት አንፃር ለማህበረሰቡ በተለይም ለገጠሩ አርሶና አርብቶ አደሩ ኀ/ሰብ እየተደረጉ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ውጤታማ ከማድረግ አንጻር የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ከማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት በመስራት የበኩላቸውን ድርሻ ሊጫወቱ እንደሚችሉ ስለሚታመን የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች በጋራ ሊሰሩበት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ቢቻል ውጤቱን የበለጠ ስኬታማ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተለይም ወቅቱ አርብቶ አደሩ ለአንስሳቱ የግጦሽ አና የውሀ ፍላጎት ለማሟላት ከቦታ ቦታ ሚንቀሳቀስበት በመሆኑ ለበሽታው ተጋላጭ ሊያደርጋቸው አና እንዲሁም ለቫይረሱ ስርጭት አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ስለሚችል አነዚህን የማህበረሰብ ከፍሎች ከኮረና ቫይረስ ለመከላከል አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የማከናን ፣ እንዲሁም በጤና ሚኒስትር እየተሰጡ ያሉ ምክሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ድጋፍ ቢደረግላቸው የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ከመግታት አንፃር ከፍተኛ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ማህበራችን ያምናል።
  1. ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለኮረና በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስኬት በመንግስት እየተሰጡ ያሉ መመሪያዎችንና ምክሮችን ሁሉም ማህበረሰብ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ለኮረና በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ስኬት አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ በዚህም ረገድ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተሰማሩት የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የማህበራችን አባላት በመንግስት የተሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግና የስራ ቦታቸውን የCOVID-19 ወረርሽኝን ስርጭት ሊገታ በሚችል መልኩ በማደራጀት ያላሰለሰ ሞያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አስፈላውን ጥረትና ድጋፍ መስጠት ተገቢ ነው፡፡   
  1. ምንም እኳን አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ በCOVID-19 በሽታ ስርጭት ዙሪያ የቤት እንስሳት ሚና ግልፅ ባይሆንም፣ የማህበረሰቡን ጤና ከመጠበቅ አንፃር፣ በተለይም የአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ እንስሳት ግብይት የሚከናወንበት ጊዜ በመሆኑ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ማህበሩ የሚከተሉትን ምክረ ሐሳቦች ይሰነዝራል፤
  • በእንስሳት መገበያያ ቦታዎች ሊፈጠር የሚችል ከፍተኛ መጨናነቅ በሽታው ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንዲተላለፍ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር ስለሚችል ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ሌሎች የግብይት መድረኮችን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት በእንስሳት ገበያ ቦታዎችም ላይ ተግባራዊ በማድረግ ሊፈጠር የሚችለውን ስጋት መቀነስ ፣
  • የእንስሳት ተዋፅዖ ማለትም ስጋ፣ እንቁላል፣ ወተት እና ሌሎችም ምርቶችን የሚያቀርቡ ቄራዎች፣ አምራቾች፣ አርቢዎች፣ ነጋዴዎች፣ አቀነባባሪዎች የኮረና በሽታን ከመከላከል አንፃር ከምን ጊዜውም በላይ አለም አቀፍ መስፈርቶችን በተከተለ ጥብቅ የአመራረት እና የምርመራ ሂደት በማከናወን፣ የባለሙያዎቻቸውን ጤና በመጠበቅ እና ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ለማህበረሰቡ ጤናማ የሆነ የስጋ እና ሌሎች የእንስሳት ተዋፅዎች በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል፣ ይህም የመንግስት ትኩረትን የሚሻና ቆራጥ የሆነ የባለሙያዎችን የቀን ተቀን ሞያዊ ተሳቶፎ የሚጠይቅ መሆኑን ማህበሩ ለማሳሰብ ይወዳል፣ በአመጋገብ ረገድም ቢሆን የእንስሳት ምርቶችን በማብሰል መመገብ ተገቢ መሆኑን መገንዘብና ተግባራዊ ማድረግ  ይገባል።
  • የቤት እንስሳትን አያያዝ በተመለከተ ማህበረሰቡ አንክብካቤ ከማድረጉም በፊት ሆነ በኋላ አስፈላጊውን የግል ንፅህናውን እንዲጠብቅ ማህበራችን ምክሩን ይለግሳል፡፡    

በመሆኑም ማህበራችን በአለም የጤና ድርጅት (WHO) ፣ በአለም የእንስሳት ጤና ድርጅት (OIE) ፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስለ ኮረና (COVID-19) በሽታ ወረርሽኝ የሚወጡ መረጃዎችን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አገናዝቦ ማኅበሩ ባሉት የመረጃ ማሰራጫ መንገዶች ሁሉ ወቅቱንና ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለአባላቱ፣ ለተባባሪ ድርጅቶች እና ለማህበረሰቡ በማሰራጨት ሰፊ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ፣ እንዲሁም አስፈላጊ በሆኑ እንቀስቃሴዎች በንቃት በመሳተፍ የተጀመረውን የኮረና በሽታ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራ ለመደገፍና ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማህበር ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ዛሬን ተሻግረን የነገን ብሩህ ቀን አብረን እናያለን!

ሚያዚያ 9 2012 ዓ ም